የአርሶ አደር የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ በመመስረት አርሶ አደሩን በሁሉም አቅጣጫዎች ባለቤትና ተሳታፊ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለፀ
ነሀሴ 8/2018 ሳንኩራ ኮሚኒኬሽን
በስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ ቀበሌያትን መሰረት ያደረገ የአርሶ አደሮች የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ የምዝገባና የአክሲዮን ግዥ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለመገምገም እና በቀጣይ የትኩረት መስኮች ላይ ለመምከር ያለመ ስልጠና ነክ የግምገማ መድረክ ተካሂዷል ።
የሳንኩራ ወረዳ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንሳይቲትዩት (ATI) ጋር በመተባበር በወረዳው የተለያዩ አምራች የግብርና ልማት ፕሮጀክቶችን በስፋት እየተገበረ ይገኛል።
ከእነዚህም መካከል ባለፉት ዓመታት በሰብል ፣ በእንስሳት ሀብትና በፍራፍሬ ልማት በምርትና ምርታማነት ላይ አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ዋነኛው ነው።
ይህንኑ ስኬት መነሻ በማድረግ የአርሶ አደር የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ በመመስረት ፣ አርሶ አደሩን በሁሉም አቅጣጫዎች ባለቤትና ተሳታፊ በማድረግ ገቢውን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲቱዩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት በአቶ ወንደሰን በኩል የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ድርሻ ግዢና የአባልነት ምዝገባ ንቅናቅ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በቀረበው ሰነድ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ምንነትና ጥቅም እንዲሁም አጠቃላይ ወረዳዊ ሂደት ዙሪያ በዝርዝር የተብራራበት ነው፡፡
መድረኩ በሳንኩራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ተሚማ ሙዴ ፣ በሳንኩራ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ ሰልማን እና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲቱዩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተባባሪ አቶ አለሙ ተከተል የተመራ ነው፡፡
በመድረኩ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ሰፊ አቅም ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ጥቅም ለመቀየር የኢንዱስትሪዎች መኖርና መስፋፋት ለአርሶ አደሩ ምርት ተጨማሪ እሴት እንደሚፈጥር ተገልጿል ፡፡
የምርት መጠንና ጥራትን በመጨመር የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያው መቋቋም ፋይዳ የጎላ ስለመሆኑም ተብራርቷል፡፡
የአርሶ አደሩ የካፒታል አቅም እንዲጎልብትና የኩባንያው ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥ የአክሲዮን ግዥው በአግባቡ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያም የተጀመረው የአርሶ አደሮች የአክሲዮን ምዝገባ አፈጻጸም ፈጣንና ስኬታማ እንዲሆን፣ እንዲሁም ኩባንያው ወደ ሙሉ ስራ ገብቶ አርሶ አደሩን የገበያ ተጠቃሚ እንዲያደርግ የየደረጃው አመራርና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል።